አርባ ምንጭ ነሐሴ 15 / 2017 ዓ.ም. (ጋሞ ቴሌቪዥን)
በጋሞ ዞን በ2018 በጀት አመት በ118 ሺህ ሄክታር ላይ ከሚለማ ምርጥ ዘር 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱ ተገለፀ።
በዞኑ የ2018 በጀት አመት የምርጥ ዘር ብዜት ማስጀመሪያ መርሃግብር በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶኮ ዮይራ ቀበሌ በይፋ ተጀመረ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማጌሶ ማሾለ እንዳሉት በዞኑ በ2018 በጀት አመት 118 ሺህ ሄክታር ላይ ምርጥ ዘር ይለማል።
ከዚህም 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱ ኃላፊው ገልፀዋል።
በዋና ዋና ሰብሎች ደግሞ ስንዴ፣ገብስ፣ጤፍ፣አተር እና ቦሎቄ 8 ሺህ 775 ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን ተናግረዋል።
ከሚለማው መሬት ውስጥ ከግማሽ በመቶ የክላስተር እርሻ እንደሆነ ጭምር ነው አቶ ማገሶ የገለፁት።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የአርባምንጭ ዕፅዋት ክሊኒክ ማዕከል ኃላፊ አቶ ሙሉአለም መርሻ አርሷአደሩ በቴክኖሎጂ ከመደገፍ ባለፈ ምርጥ ዘርን በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በግብርናው ዘርፍ ላይ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ለአርሷአደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይስማ ከተማ በበኩላቸው በአካባቢው አብዛኛው ማህበረሰብ የሚተዳደረው በግብርና መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው በመኸር እርሻ አጠቃላይ 8 ሺህ 983 ሄክታር እየለማ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ክላስተር እርሻ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በስንዴ፣ በገብስና ሌሎች ሰብሎችም ጥሩ አፈፃፀም መመዝገቡን ገልፀዋል።
የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘፍኔ ዛዳ ለአርሶ አደሩ በቂ የክህሎት ስልጠና በመስጠት በሄክታር 40 ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን አስረድተዋል።
የጋሞ ዞን ህብረት ስራ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋፅዮን ዘነበ ህብረት ስራ ማህበራትን በማደራጀት የግብርናውን የምርጥ ዘር ብዜት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከ300 ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ብዜትን በማቅረብ ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጣውን ለመተካት እየተሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።