የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ ።
በጋሞ ዞን የተፈጥሮ ሀብትን መሰረት ያደረገ የመስኖ ልማትን ለማጎልበት እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
አርባ ምንጭ : ጥር 12/2017 ዓ.ም (ጋሞ ቴሌቪዥን )
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ” በሚል መሪ ሀሳብ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና በአርባምንጭ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ለተሳታፊዎች በኦን ላይን የታገዘ ስልጠና አቅርበዋል። በስልጠናው ዙሪያም ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በተለያዩ መዋቅሮች የግብርና ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ አኳያ ፣ በመስኖ ልማትና እንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በምርጥ ዘርና ግብዓት አቅርቦት፣ በሌማት ትሩፍት አፈፃፀም በኩል የሚታዩ ክፍተቶች በቀጣይ መስተካከል እንዳለባቸው በውይይቱ ተነስቷል።
የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማጌሶ ማሾሌ በግብርና ምርትና ምርታማነት የተሻለ አፈጻጸም ያመጡ መዋቅሮች የበለጠ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል ።
ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ጥሩ አፈጻጸም ካላቸው መዋቅሮች ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በዞኑ የተፈጥሮ ሀብትን መሰረት ያደረገ የመስኖ ልማትን ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ማጌሶ የገለፁት ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ ከመድረኩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል ።
ክልሉ አዲስ ቢሆንም በግብርናው ዘርፉ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለፁት ዶ/ር መሪሁን ፤ የእርስ በእርስ ግንኙነት ፣ ትምህርትና ስልጠናዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮች መቀረፍ አለባቸው ያሉት ዶ/ር መሪሁን ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
