የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛው የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ልማት ፕሮግራም የምዘና ውድድር በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ በመካሄድ ላይ ሲሆን በውድድሩ መክፈቻ እና ሁለተኛው ቀን ላይ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡
በመክፈቻው ዕለት በሁለቱም ፆታ የተደረገው የ1000 ሜትር የሩጫ ውድድር በጋሞ ዞን ፍጹም የበላይነት ተጠናቋል፡፡
የጋሞ ዞን ልፁክ በወንዶች ከአንደኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በመያዝ የወርቅ፣ የብር እና የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን በሴቶች የወርቅ መዳሊያ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በፓራ ኦሎምፒክ ስፖርቶች በተደረገ የአሎሎ ውርወራ ውድድር የጋሞ ዞን በወንዶች እና በሴቶች ሁለት ወርቅ፣ ሁለት ብር እና አንድ ነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኑንም የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ተሳትፎ እና ውድድር ዳሬክተር አቶ ህይወት በቀለ ገልጸዋል፡፡
በዚህም የጋሞ ዞን በመጀመሪያ ቀን ውሎው 4 ወርቅ፣ 3 ብር እና 2 ነሃስ በአጠቃላይ ዘጠኝ ሜዳሊያወችን ማሸነፍ ችሏል፡፡
ውድድሩን በአሸናፊነት የተወጡ አትሌቶች በተለይም ለጋሞ ቴሌቭዥን በሰጡት እስተያየት ለማሸነፍ በመወዳደራቸውና በፅናት በመትጋታቸው ለዚህ እንደበቁ ገልጸው ክልሉን ወክለው በሀገር አቀፍ መድረክም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተነሳሽነነት እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል፡፡
የጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታመነ ተስፋዬ የጋሞ ዞን ክልሉ ባዘጋጀው 8 የስፖርት አይነቶች 200 የሚደርሱ ስፖርተኞችን ማሳተፉን ገልፀው ሁሉንም የዞኑን መዋቅሮች በማሳተፍ ሰፊ የዝግጅት እና የምልመላ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡
በዞኑ በፕሮጀክቶች ታቅፈው ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ታዳጊዎች ልዩ እድል የፈጠረ ውድድር መሆኑን ጠቁመው ይህም ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር ህብረተሰቡ ከስፖርቱ ልማት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ስድስት ቀናትም በአትሌትክስ ፣ ቮሊቦል ፣ ጠርጴዛ ቴኒስ፣ ፖራሊምፕክ ፣ እግር ኳስ ፣ በቦክስ ፣ ወርልድ ተኳንዶ እና ውሃ ዋና የስፖርት አይነቶች የምዘና ውድድሩ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
