አርባምንጭ ጥር 13/2017ዓ.ም(ጋሞ ቴቪ
አንደኛው ዙር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታዳጊ ወጣቶች ስፖርታዊ ስልጠና ልማት ፕሮግራም የምዘና ውድድር ሂደት ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ ተተኪ ስፖርተኞች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የመንግስት ቀዳሚ ግብ መሆኑን በመርሃ-ግብሩ መክፈቻ ተናግረዋል።
በክልሉ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች አቅም ያላቸው ተወዳዳሪዎች መኖራቸውን ገልፀው ከስፖርት ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ውድድሮች መዘጋጀታቸው ትልቅ ሚና እንዳላቸው አቶ ኦላዶ አስረድተዋል፡፡
ላለፉት አራት አመታት የምዘና ውድድሩ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰው ውድድሩ ዳግም መጀመሩ ለስፖርተኞች በክለቦች የመታቀፍ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጎበዜ ጎዳና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች የሚስተዋሉ የውጤት መቀዛቀዞችን ለመቅረፍ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ማድረግና አደረጃጀቶችን ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ አዘጋጅነት ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ክልሉን የሚወክሉ ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ለመመልመል ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ የውድድር እና ስነስርዓት መመሪያዎች፤በዳኝነት፣ ሽልማት እና የእድሜ ገደቦች ዙሪያም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በክልሉ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ልማት ፕሮግራም ከተጀመረ አስራ ሁለት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን ክልሉ በ11 የስፖርት ዘርፎች በሀገር አቀፍ የምዘና ውድድር ተሳታፊ እንደሚሆን ተመላክቷል።
