ለአዕምሯዊ ዉጤቶች አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሰልጣን አስታወቀ ።
ባለስልጣኑ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ሥርዓት እና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ ዉይይት በአርባምንጭ ከተማ አካሂዷል።
አርባምንጭ ፣ጥር 13 /2017 ዓ.ም (ጋሞ ቴሌቪዥን)
በዉይይት መድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አስተባባሪ አቶ አብሪድ ሰሜካ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችለው የአዕምሯዊ ንብረት አስፈላጊው ጥበቃ ባለመደረጉ ምክንያት የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤት ይሁን መንግስት ተገቢውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ገልፀው፤ ለዚህም የግንዛቤ ማነስ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለዋል።
አስተባባሪው አክለዉም ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ከማቅጨጩ በተጨማሪ በህገወጥ ተግባር ለተሳተፉ ግለሰቦች ዋነኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ በመምጣቱ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለዉጦች የመጡ ቢሆንም ለዘላቂ ለዉጥ ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተዉ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ባለድርሻ አካላት የወሰዱትን ስልጠና ተግባር ላይ በማዋል በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ሥርዓት ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን ለማስተካከል መስራት እንዳለባቸው አቶ አብረድ አስገንዝበዋል ።
ብዙ ጉልበትና ገንዘብ ወጭ ተደርጎባቸው ከሚሰሩ የአዕምሯዊ ንብረቶች ባለሙያው ተገቢውን ጥቅም ባለማግኘቱ ለከፍተኛ ኪሳራና የስነ – ልቦና ዉድቀት እየተዳረገ በመሆኑ ስልጠናው ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ያለመ ነዉ ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ ዮናስ ናቸዉ ።
ጋሞ ዞን ከፍተኛ የባህል ፣ የኪነ ጥበብና የፈጠራ ባለቤት ያለበት አከባቢ ቢሆንም በዛዉ ልክ እዉቅና ያላገኙ ተግባራት መኖራቸውን የጠቀሱት የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙናዬ ሞሶሌ ስልጠናው መሰል ችግሮች ዳግም እንዳይታዩ ያግዛል ብለዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከስልጠናው የወሰዱትን ወደ ተግባር ለመለመጥ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።