ሚዲያዎች የሐሰት ትርክትን በመመከት፣ የሀገራችንን የዕድገት አውዶች ማሳየት አለባቸው – ለገሠ ቱሉ(ዶ/ር)

አርባ ምንጭ፦ ነሀሴ 7/2017 ዓ.ም (ጋሞ ቴሌቪዥን)

የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የሐሰት ትርክትን በመመከት፣ የሀገራችንን የዕድገት አውዶች በማሳየት ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸውን ይዘቶች ማምረት እንዳለባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት(ኢቢሲ) በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ(አፕ) በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል።

በመድረኩ የተገኙት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) እንደገለጹት የኢቢሲ ዲጂታል አሠራርና የይዘት ስብጥር የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ እና ለሌሎችም ሚዲያዎች አዲሱን ምዕራፍ የከፈተ ነው።

መረጃ የሰዎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ በብዙ መልኩ በሚዳስስበት በዚህ ጊዜ፣ ኢቢሲ መረጃን በተለያዩ አማራጮች የሁሉንም መልክ በሚያሳይ አግባብ ተደራሽ ማድረጉ ለኢትዮጵያ ሚዲያ አዲስ ለውጥ መሆኑንም አስረድተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ በሰከንዶች ልዩነት ዓለምን በሚያካልልበት በዚህ ጊዜ የተዛቡ ትርከቶችን የሚያስተላልፉ በርካቶች እንዳሉም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ይህን መቀልበስ የሚችሉ፣ የሀገርን መልክ የሚገነቡ፣ ዜጎችን የሚያቀራርቡና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ይዘቶችን ኢቢሲ በዲጂታሉ ዓለም የሚያደርስ አሠራርን ማጎልበቱ ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን የሐሰት ትርክትን በመመከት፣ የሀገራችንን የዕድገት አውዶች ማሳየትና ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸው ይዘቶች ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም ማሳሰባቸውን ኢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።

ለዚህም ኢቢሲ ከ10 በላይ የይዘት ምንጮችን ከ25 በላይ ዲጂታላይዝድ ሲስተሞችን ተጠቅሞ ተደራሽ ለማድረግ የጀመረው ጉዞ ትልቅ ማሳያ ነውም ብለዋል።

ኢቢሲ ወደ ዲጂታል ምዕራፍ ሲሸጋገር አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁሉም ባለድርሻዎች ምስጋና ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው ኢቢሲ ወደ ሁሉም ኢትዮጵያና አፍሪካ እንዲደርስ በሰፊው እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው የዲጂታል ኢቢሲ ይፋ መሆንም ሰፍቶ የመድረስ ፍላጎታችን መገለጫ ነው ብለዋል።

የኢቢሲ ይዘቶች ዋና ማጠንጠኛ ኢትዮጵያዊያንን የሚያቀራርቡ፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችሉ እና የሪፎርም ሥራዎችን የማግባባት ሥራዎች እንደሆኑም አብራርተዋል።

መልካም አስተዳደርን በተመለከተ የሕዝቡን ቅሬታ የሚዳስሱ አንደ ዐይናችን ያሉ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የሕዝብ ቅሬታ የሚፈቱ በርካታ መረጃዎችን እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።#ኢዜአ

By admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *